አዶኒራም ጀድሰን
By: Dr. Girma Bekele
“የክርስቶስ መስቀል ለዘላለም ከፍ ብሎ እስከሚታይ ድረስ አገረ በርማን አልተውም።”
“በዐይናችን ፊት ሞት ልጃችንን ነጠቀን፤ ሆኖም ሐዘን በሌለበት ሰማይ ዳግመኛ እንደማገኘው እምነቴ ሙሉ ነው።”
“ፈተናው ልቤን አድምቶታል፤ መከራ የእምነት ትምህርት ቤት መሆኑን ተገነዘብሁኝ። የስቃዬን በትር በምስጋና ሳምሁት፤ በርቱንም የያዙትን የልዑል እግዚአብሔር እጆች ባረክኋቸው . . . ሐዘኔ የከፋ ቢሆንም እግዚአብሔር ከላከኝን ሥራ ላለማፈግፈግ ጨከንሁኝ። ሐዘኔ ከንቱና ትርጕም የለሽ ሳይሆን ቀጣዩን ሥራዬ የሚቀደስ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነው።”
ከፍ ሲል ያተጠቀሱት ሁለት ማስታዋሻዎች የጻፉት ወጣቶች የመጀመሪያ ልጃቸውን በወሊድ መካከል ያጡት ሚስዮናውያን አዶኒራም እና ባለቤቱ አን ጀድሰን ናቸው። ወቅቱ እ.አ.አ ወርሃ ሐምሌ 1813 ነበር። ቦታው ከሰሜናዊ ምስራቅ የሕንድ ወቅያኖስ ጋር በሚገናኘው የቤንጋል ባሕረ ሰላጤ ላይ ነበር። ይህም የሆነው በስደት ምክንያት ከሕንድ ከልካታን ትተው ወደ በርማ ባቀኑበት የ ሦስት ሳምንታት የመርከብ ጕዞ ላይ ሲሆን ልጃቸውንም እዚያው ውቅያኖስ ላይ ገንዘው ቀበሩት። በጥልቅ የሐዘን ጨለማ መካከል የተጻፉ የመጽናናት ቃሎች ናቸው።
እ.እ.አ የካቲት 19, 1812 ከሳሌም ማሳቹሰተስ ባሕር ዳር በጊዜው የብሪታንያ ምስራቅ ሕንድ ካምፓኒ ያስተዳድር ወደ ነበረው የቤንጋል ግዛት በአሜሪካ የውጭ ሚስዮናዊ ኮሚሽን ቦርድ ሲላኩ የአስራ አምስት ቀናት ሙሽራዎች ነበሩ። ከአራት ወራት የመከርከብ ጕዞ በኋላ የተቀበለቻቸው ካልካታ የብሪታኒያ ሕንድ የሚባለው ቅኝ ግዛት መናገሻ ነበረች። እንደ አን አገላለጽ “ሕመም፣ ሐዘንና መንፈሳዊ ዐይነ ሥውርነት የነገሠባት የጨላማ ምድር ነበረች”።
ካምፓኒው ከፍተኛ የሆነ የሐር፣ የጨርቃ ጨርቅ፤ የማዕድን፣ የሻይና የቅመማ ቅመም ንግድ ላይ የተሰማራ ድርጅት ሲሆን ከነበረው ዐቅም የተነሣ የአካባቢውም አሰተዳደር ነበር። የሚስዮናውያኑ አገልግሎት ሃይማኖታዊና ፓለቲካዊ ውጥረት ያስነሣል በሚል የጥቅም ሥጋት ሳቢያ ከግዛቱ እንዲወጡ ባዘዘው መሠረት ነበር አዶኒራም ከነፍሰ ጡር ባለቤቱ አን ጋር ወደ በርማ (የአሁኑ ሜይንማር) ለመሄድ ተገደዱ። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የመጀመሪያ ልጃቸውንም ያጡት ወደዚያ እያቀኑ ባሉበት አስቸጋሪ ጕዞ ላይ ነበር።
አዶኒራም ጀድሰን ከአን ሐሰልቲን ጋር የተገናኙንት ከአንዶቨር ሴሚናሪ (በአሳዛኝ ሁኔታ እያደር ግራ ዘመም የሆነው የአሁኑ አንዶቨር ኒውተን ሴሚናሪ፣ ዬል) እንደ ተመረቀ ለሚስዮናዊነት ዝግጅት ላይ ባነበረበት ወቅት ነበር። እግዚአብሔርን የምትፈራና ለወንጌል የተሰጠ ልብ ነበራት። “በወንጌል የመከራ አጋሬ” ብሎ ነበር የሚጠራት። ደግሞም ስለውበቷ እንዲህ ይላል፦ “ውበቷ የውስጥ የውጭ ብቻ አልነበረም። የነፍስና የአእምሮም ነበር። ብዙ ሳትናገር ያለችበት ቦታ ሁሉ መገኘቷ ይሰማል። ፍቅር የያዘኝ ከውበቷ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጥልቅ መንፈሳዊነቷም ጋር ነበር። የረጋ መንፈስ፣ ድፍረትና ለጌታ ሥራ የነበራት ያልተቆጠበ መሰጠት በእውነተኛ መልኩ የልቤ ወዳጅ አድርገዋታል። ልጃቸውን እንዲድሩለት ለአባቷ የጻፈው ደብዳቤ በእጅጕን ልብ ያባባል፦
“የተከበሩ ዮሐንስ ሐሰልቲን፣ ልጆን ላገባ ወስኛለሁ። የእርሶንም ይሁንታንና በረከት እሻለሁ። ሆኖም በጐ ፈቃድዎ እንደ ተጋባን ሚስዮናዊ አጋሬ በመሆን አገራችንን ትተን የምንሄድ መሆኑንን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን እፈለጋለሁ። ውድ ልጆዎ መከራና ስቃይ ዕጣ ፈንታዋ እንደሚሆን፤ ነፋስና ቁጠኛ ማዕበል የነገሥበትን የሕንድ ውቅያኖስን በቀንና በለሊት አብራኝ እንደምታቋርጥ፤ ሐሩር፣ ወረርሽ፣ ሕመምና መሰደደ እንደሚጠብቃት፤ ምናልባትም የስቃይ ሞት እንደሚጠብቃት፤ ጌታ በክብር እስኪመለስ ድረስ ዳግመኛ ላትተያዩ እንዲሚችሉ የተገነዘብ ይሁንታ መሆን አለበት። ይህን ሁሉ ዋጋም የምትከፈለው በክርስቶስ የቤዝዎት ሞት ለብዞዎች ከኀጢአት ጨለማና ከዘላለም ሞት ለመዳን መሆኑን፤ ለእግዚአብሔር ክብር፣ እንዲሁም በእርሱም መንግሥት የጽቅና የምስጋና አክሊል እንደሚጠብቃት በማሰብ የተደረገ ይሁንታ ሊሆን ይገባዋል። የተከበሩ ሐሰልቲን ይህን ሁሉ በመስማማት ልጆን ይድሩልኛል? መልስዎን በጽሎት እጠብቃለሁ።” አክባሪዎ አዶኒራም ጀድሰን። (Courtney Anderson, To the Golden Shore: The Life of Adoniram Judson (Valley Forge, PA: Judson Press, 1987, p 83.)
ይህን ደብዳቤ የላከው ወርሃ ጥር 1811 ነበር። አን 23 ዓመቷ ነበር። ቅዱሳን እስቲ እንድ ጊዜ ቆም ብለን እናስብ! በእኔ ውድ ልጄ ማኅሌት ዕድሜ ማለት ነው። እኔ ብሆን እሺ ስለማለቴ እርግጠኛ አይደለሁም። እጅግ ሞግቶ ይዞኛል። በብዙ እንባና የተጨነቀ ልብ ውሳኔው ለልጃችው ተው። የጌታ ፈቃድ ነበረና እርሷም የአዶኒራንን ጥያቄ በደስታ፣ በዕደለኝነት መንፈስና፣ በምስጋናና በጸጋ ተቀበለች። ልድያ ለምትባል ወዳጇ የጻፈቸው ማስታወሻ እንዲህ ይነበባል፦
“ምቾትን፣ ደስታን፣ ዘመዶቼንና ጓደኞቼን ሁሉ ትቼ እግዚአብሔር ያሰበውን ሁሉ ለማከናወን መግቦቱ በመታመን ወስኛለሁ . . . የሚገጥመኝን መከራ ሁሉ የምችልበትን አንዲሁም በእኔ ሊፈጽም ያሰበውን ሥራ ሁሉ ማድረግ የምችልበትን ጸጋ እግዚአብሔር እንደሚሰጠኝ እምነቴ ጽኑና ሙሉ ነው። በፍጹም አይተወኝም፤ አይጥለኝም።” (Francis Wayland, Memoir of the Life and Labors of the Rev. Adoniram Judson, D.D., Vol. 1 (Boston: Phillips, Sampson & Co., 1853, p. 27)
ይህም ቍርጠኝነት የሐዋርያው ጳውሎስን ያስተውሰኛል፦
“አሁንም እዚያ ስደርስ የሚደርስብኝን ባላውቅም፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው። ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም، ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።” (ሐዋ. 20፥22-24)
ለ አንድ ዓመት ያህል የኖሩበትን የከልካታን ምድር በስደት ምክንያት ለቅቀው በርማ የገቡት ዕለተ ሐምሌ 13፣ 1813 ነበር። እንግዲህ በዚሁ ጕዞ ላይ ነበር እንደተወለደ የሞተውን የበኵር ልጃቸውን ያጡት። ብሕሩ ላይ ሲቀብሩ የተጽናኑበት ቃል፣ “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን” (ኢዮብ 1፥21) የሚለው ነበር። ራንጉን (የአሁኑ ያንጉን) ከተማ እጅግ የተረሳና ከባድ የመከራ ቦታ ነበር። ፈጽሞውኑ ወንጌል ያልሰማ ሕዝብ የሚኖርበት በርሓ ነበር። ሕክምና፣ መንገድና ውሃ የሌለበት። የኮሌራ፣ የወባና የውሃ ወለድ ወረርሽኝ የሚያጣቀውና ከሥልጣኔ እጅግ የራቀ ከተማ ነበር። አን እንዲህ ትላለች፦ “ለባዕድ አምልኮ ሙሉ ለሙሉ ዐልሮ የተሰጠ፤ ፈጽሞውኑ የጨለማ ግዛት ነበር። የምናውቀው አንድም ወዳጅ አልነበረንም። ሆኖም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነበር።” (Memoir, p. 113.)
የበርሚስን ቋንቋና ባህል መልመድ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነበር። ስድስቱ ዓመታት ያለፉት ቋንቋ በመማር፣ በጸሎት፣ በገበያ ቦታ በመመስከርና ትራክት በማዘጋጀት ነበር። ጤናቸው እየተናጋ፣ በተለይም የአን፣ ብዙ ጊዜ የሞት አፋፍ ደረሳ ተመልሳለች። የጳውሎስ ሐዋርያዊ ጕዞና መከራው እጅግ ያጽናናቸው ነበር። መከራን ያሰተናገዱበትን ልብ ሳስብ ቀጥሎ ያለው ቃል ይገልጥልኛል፦
“ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ، ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።” (2 ቆሮንቶስ 4፥16-18)
ብርቱ ጸሎታቸው، አዶኒራም እንዳለው “ለብዙ ጸጋና ታማኝነት” ነበር። ትኵረቱ በግል ጥረት ስኬታም መሆኑ ሳይሆን በታማኝነት እንደ ቅዱስ ቃሉ ለእግዚአብቤር ክብር መኖርና በትጋት ወንጌልን ማገልገል ነበር። በሰው ሚዛን ፍሬያማ ባይመስልም እንኳን፣ በብዙ ተቃውሞ፣ ስደትና ተስፋ አስቆራጭ ከባድ ሚስዮናዊ የአገልግሎት ጕዞ ውስጥም ለታመነው ጌታ ራሱን ዐሳልፎ በመስጠት የዕለት ተዕለት ሥራውን በትጋት ያከናውን ነበር። የጋቱን ውጤቱን ለጌታ ሉዐላዊነተ የተወና የታዘዘ ሕይወት ነበረው። ሚሊዮኖች ጌታ ሳይውቁ የመጥፋታቸው ጕዳይ ትልቅ የዘወትር ሸክሙ ነበር። “አንድም ሰው ጌታ ሲቀበል ላላይ እችላለሁ። ሆኖም በሌላ ቦታ የንጕሥ ያህል ዝና، ክብርና ሐብት ከሚኖረኝ እዚሁ በድኽነት، በብቸኝነት، በስደት، በመከራና በሞት ጥላ መካከል የጌታን ሥራ በታማኝነት መሥራት የዘላለም ዕድልና ፈንታዬ አድርጌ መርጫለሁ። (Memoir, vol. 1, p. 147)
ምስጋና ጸጋ የሞላው ይህ የመሰጠት ጥግ ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸው ዐይነት ነው፦
ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁል ጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና። እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ። (2 ቆሮንቶስ 4:8-12)
የአዶኒራም ቁርጠኛ ውሳኔ “የክርስቶስ መስቀል ለዘላለም ከፍ ብሎ እስከሚታይ ድረስ በርማን አልተውም” የሚል ነበር። (Memoir, Vol. 1, p. 109. “ - “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን ሁሉ፣ ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና። (ዕን. 2፥ 14) የሚለው ቃል ሚስዮናዊ አርማው ነበር። ግንቦት 4፣ 1816፣ በበርማ የበኩር ልጃቸው የነበረው ሕጻን ሮጀርስ በትኵሳት ንዳድ ሕይወቱ ዐለፈ። ሰባት ወር ከ 23 ቀኑ ነበር። የአን ማስታወሻ አንዲህ ይላል፦
“በመመርና በማጉረምረም የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት አልጠየቅንም። ይልቁንም ለመከራ በትር ራሳችንን በጸጋ አሳልፈን ሰጠን።” (Knowles, James D. Life of Mrs. Ann H. Judson, Late Missionary to Burmah; With an Account of the American Baptist Mission to that Empire. Philadelphia: American Sunday School Union, 1830, p.80)
አዶኒራም ደግሞ፣ “ሮጀር ደስታችንና ፍስሐችን ነበር። እግዚአብሔር ግን ጠራው። ልባችን በሐዘን ተሰብሯል። ሆኖም ልጃችን በአዳኛንና በጌታችን ዕቅፍ መሆኑን ስናስብ እንጽናናለን።” በማለት ሐዘኑን ጽፏል። (Memoir, vol. 1, p. 138)
አዶኒራም በቀን እስከ አስራ ስደስት ሰዓት እየሠራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የማቴዎስ ወንጌልን በበርሚስ ቋንቋ አዘጋጀ። አን ደግሞ ልጆችን ማስተማር ጀመረች። ከስድስት ዓመታት ትግል በኋላ ማውንግ ናው የሚባል ወጣት ወደ ጌታ መጣ። የወንጌል የመጀመሪያ ፍሬ ሆኖ፣ ዕለተ ሰኔ 27፣ 1819 ተጠመቀ። አዶኒራም ደስታውን “አንድ በርሚስ ለክርስቶስ ተንበረከከ፤ ፍሬው መብቀሉ ይቀጣላል።” በማለት ከትቧል። በ1820 የመጀመሪያቱ አጥቢያ ተመሠረተች። በብዙ ሺሕ የሚቆጥሩ የወንጌል ትራክቶች ታተሙ። ሆኖም በአንግሎ በርሚስ ጦርነት (1824-1826) የውጭ አገር ዜጐች በሙሉ ሲታሰሩአዶኒራምም በሰላይነት ተጠርጥሮ ለ 17 ወራት አስቸጋሪ ወህኒ ቤት ተጣለ። ዕለቱ ሰኔ 8፣ 1824፤ አን ደግሞ የሰባት ወር ነፈስ ጡር ነበረች። የስቃይ ቦታ ነበር። በዚያ በረሓ ውስጥ በእግር እየተመላለስች ስንቅ ታቀብለው፤ ሚስዮናዊ ብቻ መሆኑን ተረድተው ከሞት ፍርድ እንዲተርፍ ትማጸን ነበር። ማን ሊሰማት! . . . ሆኖም አታጕረመርምም ነበር። ይልቁን እንዲህ ብላ ማስታወሻ አኑራለች፦
“ሕይወት እንዴት ሊገፋ እንደሚችል ፈጽሞውኑ አላውቅም። ያለንበት ሁኔታ ከእኔ ዐቅም በላይ ቢሆንም ባለቤቴን በእጁ የያዘውን እርሱን እታመናለሁ።” (Life of Mrs. Ann H. Judson, p. 154)
እስር ቤቱ የስቃይ ቦታ ነበር። በዚያ በረሓ ውስጥ ከግንድ ጋር በብረት ሰንሰለት የተጠፈሩት እግሮቹ ተተልትለው ነበር። ቀን እንደ ምድጃ እሳት በሚጋረፈው ሙቀት መላ አካሉ ይለበለባል። ማታ ደግሞ የወባ ትንኝ ማደሪያ ነበር። ራብ፣ የውሃ ጥምና ድብደባ ስንቆቹ ነበሩ። እነዚያን ክፉ ወራት እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦
“የነበርሁበት ሥቃይ ከቃላት በላይ ነበር። እግዚአብሔር ሉዓላዊ፤ ለፍቅሩና ለምሕረቱ ደግሞ ወሰን የሌለው መሆኑን በማመን ብቻ ነበር መከራዬን የቻልሁት።” (Edward Judson, The Life of Adoniram Judson, vol. 2 (New York: Anson D.F. Randolph & Co., 1883, p. 312)
በእግዚአብሔር ምሕረት ኅዳር 4፣ 1825 ከአቫ እስር ቤት በድንገት ተፈታ። አን እጅግ ተጐሳቍላ፣ ጤንነቷም እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነበር። እስር ቤት እያለ የተወለደችው ሕጻን ማርያም ከተመጣጠነ ምግብ ዕጥረትና ከተደጋጋሚ በሽታ የተነሣ አስጊ ደረጃ ላይ ነበረች። ከአስራ አንደ ወራት በኋላ ጥቅምት 24፤ 1826 አን ከዚህ ዓለም ሥቃይ ዐረፈች። ከስድስት ወራት በኋላ ሕጻን ማርያም ተከትላት ዐረፈች። ሚያዝያ 24, 1827። ሁለቱንም ተራ በተራ በግቢያቸው ውስጥ የቀበረው በእጁ ነው። እንዲህ ይላል፦
“የምትወደውን የወንጌል ሥራ ለእኔ ዐደራ ትታ ወደ ዘላለም ዕረፍት ገብታለች።” (Memoir , Vol. 2, p. 20)
“ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (የሐ. 14:1-2)
በብዙ ብቸኝትና በጥልቅ ድባቴ መካከልም، ባይገባውም በመከራው የክርስቶስን ሥራ እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት ነበረው። ጭንቀቱን፣ ብቸኝነቱንና መረሳቱን ከጌታ ጭንቀትና መከራ አንጻር ነበር የሚያየው። በተለይም ይህ የጌታችን ቃል ለእርሱ ትልቅ ትርጕም ነበረው፦
“እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል። “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚህች ሰዓት ብታድነኝስ? ይሁን፤ የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው!” (ዮሐ. 12፥24-28)
አን ካረፈች ከስምንት ዓመታት በኋላ، ሣራ ቦርድማን ከምታባል ሚሲዮናዊት ጋር ተጋቡ። ሣራ ቀደም ሲል ልክ እንደ እርሱ የትዳርና የወንጌል አጋሯን ያጣችና የአንድ ልጅ መበልት የነበረች ስትሆን، በቋንቋ ችሎታና በወንጌል ሥርጭት እጅግ የተባረከች ነበረች። ሆኖም ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ በሳንባ ነቀርሳ ተመትታ ለሕክምና ወደ አሜሪካ በመንገድ ላይ እያሉ ዐረፈች። የተቀበረቸውም ደቡባዊ አትላነቲክ ውቅያኖስ ግዛት ውስጥ ባለች ሴይንት ሄሌና ደሴት، መስከረም 1، 1845 ነበር። በዚሁ አጋጣሚ አዶኒራም ወደ አሜሪካ የተመለሰው ከ 33 ዓመታት በኋላ ሲሆን በዕረፍት ላይ እያለ ኤምሊ ቸባክ ከምታባል እኅት ጋር ተዋወቀ። ሰኔ 2، 1846 ተጋብተው ወርሃ ኀዳር، 1846 በርማ ግቡ።
ኤምሊ ወጣትና በ28 ዓመት ታናሹ ብትሆንም ብርቱ የወንጌል አገልጋይ ነበረች። ለአዶኒራም ብዙ ፍቅርና አክብሮት ነበራት። ተራ በተራ ወደ ጌታ የሄዱትን የአንና የሣራን መከራና ዕጣ ፈንታ እያወቀች አዶኒራምን በማግባት የወንጌሉ ሥራ እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጋለች። ከእርሱ የወለደችው አንድ ልጅ ብቻ ሲሆን، ከሣራ የተወለዱትና ከሞት የተረፉትን ሁለት ልጆቹን አሳድጋለች። አብረው የኖሩት ወደ አራት ዓመት ያህል ነበር። እንዲህ በማለት በምስጋና ማስታወሻ አኑራላች፦
“አጭር የጫጉላ ወቅት። እነዚያ አራት ዓመታት በመከራ ደመናና በደስታ የማለዳ ፀሐይ የታጀቡ ነበሩ ሆኖም ለምዕተ ዓመታት ደስታ የሚሰጠኝ ሌላ ዕድልና ቦታ ቢኖር እንኳን አልቀይራቸውም።” (Memoir, vol. 2, p, 338)
ዓርብ ሚያዝያ 12، 1850 አዶኒራም ጀድሰን ወደ ጌታ ሄደ። የመጨረሻዎቹን ወራት መተንፈስ ይቸገር ነበር። ምናልባት የአየር ለውጥ ይረዳ ይሆናል በሚል ተስፋ ወደ ፈርንሳዊቷ ደሴት ሞርሸት እየሄደ ሳለ ነበር በቤንጋል ባሕረ ሰላጤ ላይ በድንገት ያረፈው። የመጀመሪያ ልጁ የተቀበረበት እዚያው ባሕር ላይ ነበር አስከሬኑ ያረፈው! የመጨረሻ ቃሉም፦
“በቀኑ መጨረሻ ላይ ከትምህርት ቤት እንደ ተለቀቀ ልጅ، በደስታ እሄዳለሁ።” (Judson, The Life of Adoniram Judson, vol. 2, p. 499)
አዶኒራም ለቃሉ የበላይነት ፈጽሞውኑ የተሰጠና የጸሎት ሰው ነበር።
“በማንኛውም መንፈሳዊ ጕዳዮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የባለይ ባለሥልጣን ነው። ሳይገባኝ ሲቀርና መረዳቴም ውሱን ሲሆንም የእግዚአብሔር ቃል የጸና ነው። ብያኔዬም ስሑት ሲሆን، ቃሉ ይመልሰኛል። በብቸኝነት እውነትንና ጥበብን ሁሉ ያያዘ መጽሐፍ ነው። ( Edward Judson, The Life of Adoniram Judson, 1883, vol. 1, p. 87)
ስለ ብርቱ የጸሎት ሕይወቱ አን እንዲህ በማለት ጽፋ ነበር፦
“ፀሓይ ሳተወጣ، ቤቱ ጸጥ እንዳለ በማለዳ ለሰዓታታ በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክኮ ልቡን ያፈሳል። ስለ ጌታ ሥራና ስላልዳኑ ነፍሳት አጥብቆ ይጸልያል . . .።” (The Life of Mrs. Ann H. Judson, , p.112).
አዶኒራም የስንዴ ቅንጣት ነበር። “በባሕር ውስጥ ተተቀብሯል። ሕያው ሥራው ግን በበርማ ተራራዎች ላይ ከፍ ከፍ ብሎ ይታያል።” (Boston Recorder, August 1850)። ጥር 31، 1834 ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም ሥራውን አጠናቀቀ። በመከራ የታሸ የ21 ዓመታት ትጋት ውጤት ነበር። ቃለ እግዚአብሔር፤ ትልቅና ምትክ የለሽ ስጦታ። በርሚስ ብርሃን በርቶላታል። ዛሬ በሜን ማር ባፕቲስት ኮንቤሽን ሥር 5500 አብያተ ክርስቲያናትና 1.7 ሚሊዮን ወንጌላውያን አማኞች አሉ። የአዶኒራም ምስክርነት ቢያንስ ለሐደሰን ቴይለር، ለዴቪድ ሊቪንግስተና ለኤሚ ካርማይክል ሚስዮናዊ መነሣሣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ወንጌል እኛም ዘንድ የደረሰው በብዙ መስዋዕትነት ነው። እኛስ እንዴት ነን? ወዴት እየሄድ ይሆን? አገር ቤትም፤ ዲያስፓራም? ልባችን የተያዘው በምን ይሆን? ወደ 26% የሚሆኑ ወንጌል ፈጽሞውኑ ያልሰሙ የሀገራችን ሕዝቦች አሉ። ለሶማሊ، ለአርጐባ، ለአፋር، ለስልጢ، ሐረሪ، በብዙ ክልሎች . . . ወዘተ ማን ይሂድ? ዘመናችን، የቤተ ክርስቲያን ዐቅምና ገንዘብ እንዴት እያለቀ ነው? ቅዱስ ቃሉ ስለ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲህ ይላል፦ "በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።" (2 ቆሮ. 5፥15)። ያለንበት ፈርጀ ብዙ ቀውስ ከዚህ እውነት ጋር ምን ያህል በተቃርኖ እየኖርን እንደሆነ ማሳያ ነው። በቍጥር አድገናል ሆኖም በሕይወት ምስክርነት ከፍተኛ ዝቅጠት ውስጥ እንገኛለን። እርስ በእርስ በመከፋፈል፤ በሐስት ትምህርት፤ በአመራር، በሥነ ምግባርና በሞራል ቀውስ፤ ወንጌል ዋና ባልሆነበት መባከን፤ በዘረኝነት . . . በብዙ ሕይወታችን ተሰርቋል። የቅቡልነትና የተአማኒነት ጕዳት ደርሶብናል። መመለስ ይሁንልን። እግዚአብሔርም በምሕረቱ ያስበን!
በብዙ መከራ እያለፋችሁ ለምታገለግሉ ትሩፋን የወንጌል አገልጋዮች ይህን ቃል ልተውላችሁ፦
“ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ።”(1 ጴጥ. 4፥13)